
ባልንጀራህን እንደራስህ ዉደድ…. – ማር 12፡31
ራስህን ካልወደድከዉ ህይወትን ማጣጣም ከባድ ነዉ፡፡ ራሳቸዉን እንዲቀበሉና ራሳቸዉን ሆነዉ እንዲኖሩ ያልተማሩ ሰዎች ሌሎችን መቀበልና አብሮ መሆን ይከብዳቸዋል፡፡
ሰዎችን አለመቀበሌ ችግሩ ራሴን አለመቀበሌ እንደሆነ እግዚአብሔር በቃሉ በኩል እስኪያስረዳኝ ድረስ ያሳለፍኩት ጊዜ ከባድ ነበር፡፡ ራሴን አልወደዉም ነበር!
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረዉ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ፣ መጥፎ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ያፈራል፡፡ ልክ እንደዚያዉ በህይወታችን ፍሬ የሚመጣዉ ዉስጣችን ካለዉ ሥር ነዉ፡፡ በሐፍረት፣ በጥፋተኝነት ስሜት፣ በበታቸኝነት፣ በመገፋት፣ ፍቅርና ተቀባይነት በማጣት ወዘተ ሥር ሰደህ ከሆነ የግንኙነትህ ፍሬ ስቃይ ይሆናል፡፡
ምንም ቢሆን አንድ ጊዜ የእግዚአብሔርን የማይለዋወጥ ፍቅር ሲገለጥልህ ራስህንና ሌሎችን መቀበል ትጀምራለህ፤ በሂደትም ይህ አዲስ ሥር ፍሬ ማፍራት ሲጀምር ግንኙነትህ ይታደሳል፡፡
በምን ውስጥ ነዉ ሥር የሰደድከዉ? ልብህን ዛሬ መርምርና እግዚአብሔር በፍቅር አፈር እንዲተክልህ ጸልይ ከዚያ ራስህንም ሌሎችንም በቅንነት መዉደድ ትችላለህ፡፡ በእርሱ መተከልህን ዛሬ እርግጠኛ ሁን፡፡
የጸሎት መጀመሪያ
እግዚአብሔር ሆይ አንተ ለእኔ ባለህ ፍቅር ሥር መስደድ እፈልጋለሁ፡፡ ያለአንተ ፍቅር ራሴንም ሆነ ሌሎችን መዉደድ አልችልምና ፍቅርህን ዛሬ እቀበላለሁ፡፡