ትዕግስትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍፁንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈፅም፡፡ – ያዕ 1፡4
የምንፈልገው ለውጥ በሙሉ በአንድ ጀንበር ስለማይመጣ፣ እኔና እናንተ እግዚአብሔርን ‹ለውጠን› ብለን ስንጠይቀው፣ ምን እያልን እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ዝግታ መሀል ወይም በገጠመን ተቃውሞ ውስጥ እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ቢኖር እየተለወጥን የምናድግበትን ዕድል ነው የሚሰጠን፡፡
በለውጥ ሂደት ውስጥ ስንሆን ወይም በተቃውሞ ውስጥ ስንሆን ትዕግስት እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያዕቆብ 1 ይነግረናል፡፡ ትዕግስት በመከራ ውስጥ የሚዳብርና የሚያድግ ለህይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፡፡ መፅሐፍ ቅዱስም ትዕግስት ሲኖረን ምንም የማይጎድለን እንደሆንን ነገር ግን ፍፁምና ሙሉ እንደምንሆን ይነግረናል፡፡ ትዕግስትን ለማግኘት ግን በሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካላለፍን በስተቀር ሌላ መንገድ የለውም፡፡
እግዚአብሔርን የምናገለግልና በዚህ ዓለም ላይ ልዩነትን የምንፈጥር ድል አድራጊ ክርስቲያን መሆን የምንፈልግ ከሆነ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ግድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ የምናልፍበት ሁኔታ ሁሉ መሳሪያችን እንጂ መጥፊያችን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰይጣን ባገኘው ዕድል ሁሉ ተስፋ ሊያስቆርጣችሁ ይችላል፣ እግዚአብሔር ግን ከጠላቶቻችሁ ሁሉ በላይ ስለሆነ ማንኛውንም ተግዳሮት አሳልፎ ድልን ይሰጣችኋል፡፡
ስለዚህ ዛሬ በመከራ ውስጥም እንኳን ብትሆኑ፣ እግዚአብሔር በዚያ ውስጥ እንዲሰራ ፍቀዱለት፡፡ ትዕግስታችሁም ባደገና በዳበረ ቁጥር፣ ድሉ ትልቅ ወደሆነበት ህይወት ውስጥ ትገባላችሁ፡፡
የጸሎት መጀመሪያ
ጌታ ሆይ! እንድትለውጠኝ እፈልጋለሁ፤ ይህ ማለት ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፌ የግድ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለፍኩ ጊዜ እንድፀናና እንድቆም ብርታትህን ስጠኝ፤ ያኔ ትዕግስት ይኖረኛል፣ በክርስቶስም በሙላት አድጋለሁ፡፡