
የሰው አካሄድ በእግዚአብሔር ይጸናል፤በመንገዱም ደስ ይለዋል፡፡
የክርስትና ህይወት ጉዞን ይመስላል፡፡መሪያችን መንፈስ ቅዱስ ነው..በየዕለቱ ይመራናል፡፡ሁሌም ለህይወታችን ወደሚበጀው ይመራናል፡፡ለደስተኛ እና ለውጤታማ ጉዞ ቁልፉ እሱን መከተል ነው፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔርን ማለት መከተል ምን ማለት ነው?በመሰረታዊነት ለእሱ መታዘዝ፣ምሪቱን መከተል እና የሚለውን ማድረግ ማለት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን እንቀድመዋለን፡፡ምርጡን አቅጣጫ እንደምናውቀው እናስባለን ወይም የሱን ጊዜ መታገስ ያቅተንና ፈጣን መስሎ ታይቶን መጥፎ ቦታ ላይ እንታጠፋለን፡፡መጥፎው ነገር ታዲያ አንዴ መንገዱ መውጫ እንደሌለው ስናውቅ ወደገባንበት ለመመለስ ብዙ ርቀት ወደኋላ መሄድ ይኖርብናል፡፡
መልካሙ ዜና እንደገና ሊመራን እና ትክክለኛውን መንገድ ሊያሳየን እግዚአብሔር በዚያ አለ፡፡
እግዚአብሔር እንዳንዱን ጉዟችንን ፍጹም በሆነ መንገድ አቅዷቸዋል፡፡እንደሚወደን፣መልካም እና ጻድቅ እንደሆነ እና ልንታመነበት እንደምንችል ሙሉ በሙሉ ልንረዳ ይገባናል፡፡
ለእኛ ልክ በሆነው አቅጣጫ እንደሚመራን ልናምነው እንችላለን፡፡ስንስት እንደሚያስተካክለንና ወደ ትክክለኛው ነገር እንደሚመልሰን ልንታመንበት እንችላለን፡፡በመንገዳችን ስላሉ ሌሎች ሰዎች ልንታመንበት እንችላለን፡፡ስለህይወታችን ልንታመንበት እንችላለን…በቃ፡፡
መንገዱን ስለሚያውቀው እና ሁልጊዜም ከእናንተ ጋር ስለሚሆን የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ተከተሉ፡፡ገና ሳትወለዱ በፊት ለእናንተየህይወት ዘመን ወዳቀደው መልካም ነገሮች ሁሉ እንደሚመራችሁ ታመኑበት፡፡እናም ጉዟችሁን ተደሰቱበት፡፡
የጸሎት መጀመሪያ
እግዚአብሔር ሆይ ቃልህ ሲናገር እግዚአብሔርን የሚፈሩትን እርምጃቸውን ትመራለህ ይላል፡፡ለእኔ ባለህ ጉዞ ላይ እንደምትመራኝ አምናለሁ፡፡ከመንገድ ስወጣም እንድመለስ እና ጉዞዬን እንድቀጥል ልትረዳኝ ሁልጊዜ በዛ እንዳለህ አውቃለሁ፡፡