የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ለየዋሆች፣ ለድኾች፣ በመከራ ላሉ የወንጌልን የምስራች እንድሰብክ፣እግዚአብሔር ቀብቶኛል፡፡ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ለምርኮኛች ነጻነትን፣ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል… – ኢሳ 61፡1
መጽሀፍ ቅዱስ ሲናገር ኢየሱስ የመጣው ቁስላችንን ሊፈውስ ነው፣ የተሰበረውን ልባችንን ሊፈውስ እና ሊጠግን ነው፣ በአመድ ፈንታ ውበትን፣በለቅሶ ፈንታ የደስታን ዘይት ሊሰጠን ነው (ኢሳ.61፡1-3ን ይመልከቱ) ።
ብዙ ክርስቲያኖች ይሄንን ክፍል አንብበው እግዚአብሔር ከስጋዊ እና መንፈሳዊ ህመም ሊፈውሰን እንደሚፈልግ ያውቃሉ፣ ነገር ግን ከዚህ ሌላም ነገር አለው፡፡እውነታው ስሜቶቻችን የአፈጣጠራችን አካል ናቸው እናም ልክ እንደሌላው የሰውነታችን ክፍል ሁሉ ይታመማሉ፡፡
ዛሬ አለማችን በስሜት ህመም እየተሰቃዩ ባሉ ሰዎች የተሞላ ነው፡፡ምንጩ ብዙ ጊዜ ጥቃት፣ተቃውሞ፣መተው፣መካድ፣ማዘን፣ፍርድ፣ሒስ ወይም በሌሎች የሚታዩ ሌላ አሉታዊ ባህሪያት ናቸው፡፡ይህ የስሜት ህመም ከአካላዊ ህመም የባሰ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም ሰዎች ደብቀው እውነተኛ እንዳልሆነ ሊያስመስሉ ይችላሉ፡፡
በህይወታችሁ የስሜት ጉዳት ካጋጠማችሁ ኢየሱስ ሊፈውሳችሁ እንደሚፈልግ ልታውቁ ይገባል፡፡ስለአካላዊ እና ስለመንፈሳዊ ጉዳያችሁ ብቻ ነው ግድ የሚለው ብላችሁ በማሰብ ስህተትን አትስሩ፡፡ቁስሎቻችሁን ወደ እርሱ አቅርቡ፡፡የተጎዳችሁበትን ስፍራ ሁሉ ኢየሱስ መፈወስ ይፈልጋል!
የጸሎት መጀመሪያ
ጌታ ሆይ ስሜቶቼን ጨምሮ ስለሁለመናዬ ግድ ስለሚልህ አመሰግንሀለሁ፡፡ያሉብኝ ማናቸውም የስሜት ህመሞች እና ቁስሎችን ወደ አንተ አመጣቸዋለሁ፡፡ልትፈውሰኝ እና ወደ ቀደመ ስፍራዬ ልትመልሰኝ እንደምትችል አምንሀለሁ፡፡