
ኢየሱስም፣ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽምን?” አላት፡፡ – ዮሐ 11:40
አስተዉስ ኢየሱስ ማርያምንና ማርታን የጎበኘዉ ወንድማቸዉ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን አልፎት ነዉ፡፡ በስተመጨረሻም ኢየሱስ ከደረሰ በኋላ ማርታ ያለችዉ፦ “ጌታ ሆይ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” (ዮሐ 11፥21)፡፡
ማርታ በግልጽ ተስፋ መቁረጥ ዉስጥ ነበረች፡፡ ከዚያም ኢየሱስ “ወንድምሽ ይነሳል” አላት፡፡ ማርታም “በመጨረሻዉ ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አዉቃለሁ” አለችዉ (ቁጥር 23-24)፡፡ እኔ ኢየሱስ በትክክል ምን እያለ እንደነበረ የተረዳችዉ አይመስለኝም ምክንያቱም እየተመለከተች የነበረዉ ወደ ፊት ሊሆን የሚችልን ክስተት እንጂ የዛሬን እዉነታ አልነበረም፡፡ ነገሮች እንደሚለወጡ ፈጽሞ አልጠበቀችም፡፡
ብዙዎቻችን ልክ እንደ ማርታ ነን፤ በችግሮቻችን የቆምንና እግዚአብሔር ነገሮችን ገለል ሊያደርግ እንደሚችል የማንገነዘብ ነን፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነስቶአል፤ ደግሞም በአንተ ሕይወት ያለዉን “አልዓዛር” ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ግንኙነትህን እንዲያድሰዉ ፈልገህ እንደሆነ፣ በጤናህ ወይም በፋይናንስህ ማደግ እንዲሰጥህ ፈልገህ እንደሆነ ወይም እርሱ በአንተ ሕይወት ወዳለዉ ፈቃድ እንዳትንቀሳቀስ ያገደህን እንቅፋት እንዲያስወግድልህ ከፈለግህ፤ ብቻ ማንኛዉም ፍላጎት ከእግዚአብሔር ጋር ቀላል ነዉ! (ማር 10፥27ን ተመልከት)፡፡
ተስፋ አትቁረጥ! ምንአልባት ዛሬ ላይ እየተጎዳህ ይሆናል ነገር ግን ከማንኛዉም ተስፋ መቁረጥ ዉስጥ እግዚአብሔር አዲስ ጅማሮን ማምጣት ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር እመን፤ በህይወትህ ክብሩን ሲገልጥ ተመልከት፡፡
የጸሎት መጀመሪያ
ጌታ ሆይ! በሕይወቴ ከማንኛዉም ሁኔታ ዉስጥ ለክብርህ የሚሆን ሥራ መስራት እንደምትችል አዉቃለሁ፡፡ ከችግሮቼ በማማረር ፈንታ አንተ በሕይወቴ ያለዉን “አልዓዛር” እንደምታስነሳ አምናለሁ፡፡